የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ
የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ
የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የሀገርን ኢኮኖሚ ለመገንባትና ሥራ አጥነትን ለመቀነስ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው። ዘርፉ ከሥልጠና ተቋማት ግንባታ ጀምሮ እስከ ቴክኖሎጂ ሽግግር ድረስ ሰፊ የሥራ መስኮችን የሚሸፍን ሲሆን፣ ዘርፉ ደረጃቸውን የጠበቁ የሥልጠና ተቋማትን በማስፋፋት፣ የሥርዓተ-ትምህርት ዝግጅትን በማዘመንና ብቁ አሰልጣኞችን በማፍራት የሥልጠና ጥራትን ለማረጋገጥ በትኩረት ይሠራል። ማንኛውም በዘርፉ የሚሰጥ ሥልጠና የሥራ ገበያውን ፍላጎትና የኢንዱስትሪዎችን ተጨባጭ ሁኔታ መሠረት ያደረገ እንዲሆን በማድረግ፣ ሰልጣኞች በቀጥታ ወደ ሥራ እንዲሰማሩ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል። ዘርፉ የቴክኖሎጂ ማዕከል በመሆን የፈጠራ ሥራዎችን ያበረታታል፤ አገር በቀል ዕውቀቶችን ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር ያቀናጃል፤ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማፋጠን ለኢንተርፕራይዞች የቴክኒክና የክህሎት ድጋፍ ይሰጣል። የአሰልጣኞችን፣ የአመራሮችንና የሰልጣኞችን አቅም በየጊዜው በአጫጭርና በረጅም ጊዜ ሥልጠናዎች በማሳደግ፣ ዘርፉ ከዘመኑ የዲጂታልና የአረንጓዴ ክህሎት ፍላጎቶች ጋር እንዲራመድ ያደርጋል።
በአጠቃላይ የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ “ተግባር ተኮር” የሆነ ዕውቀትንና ክህሎትን ለዜጎች በማስታጠቅ፣ ኢንተርፕራይዞችን በማጠናከርና የቴክኖሎጂ ፈጠራን በማስፋፋት ለሀገር ሁለንተናዊ ብልጽግና ወሳኝ ምሰሶ ሆኖ ያገለግላል።
በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ያሉ ዳይሬክቶሬቶች የሚሰጡ ዋና ዋና አገልግሎቶች
በተቋማት ማስፋፋትና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት የሚሰጡ ዋና ዋና አገልግሎቶች
1. ዳይሬክቶሬቱ በክልሉ የሚገኙ መሰረታዊ የመለስተኛና መካከለኛ ደረጃ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማትን ያስተዳድራል፣ ያቋቁማል፣ እንዲሁም ያስፋፋል።
2. የግል ባለሀብቶች፣ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ኅብረተሰቡ በዘርፉ የሚሳተፉበትን ስልት ይቀይሳል።
3. ለተቋማት የሚያስፈልጉ የሥልጠና ግብዓቶችን ያሟላል፤ እንዲሁም የሥልጠና መሣሪያዎች ጥገና እንዲደረግላቸው ያደርጋል።
4. ተቋማት የራሳቸውን የውስጥ ገቢ እንዲያጎለብቱና ራሳቸውን እንዲደግፉ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል።
5. የሥልጠና ጥራት መለኪያ መስፈርቶችን ወይም ስታንዳርዶችን ያዘጋጃል፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ይከልሳል።
6. ተቋማት በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት እንዲገነቡ በማድረግ የማሽነሪና የሰው ኃይል ግምገማ ያካሂዳል።
7. ለተቋማት የዕውቅና፣ የፕሮግራም ምዝገባና የዕድሳት ፈቃድ አገልግሎቶችን ይሰጣል።
8. በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት የውስጥ ቁጥጥር፣ ኦዲት፣ እንዲሁም ድጋፍና ክትትል ያደርጋል።
9. የቴክኒክና ሙያ የሥልጠና ማስረጃዎችን ትክክለኛነት ያረጋግጣል።
10. ዲጂታል እና አረንጓዴ ክህሎቶች በቴክኒክና ሙያ ሥርዓተ ሥልጠና ውስጥ እንዲካተቱ ያደርጋል።
11. የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ካውንስልና ቦርድ እንዲቋቋም ምቹ ሁኔታዎችን ያመቻቻል።
12. ለተቋማት የሥልጠና ግብዓት የሚሆኑ የማሽነሪዎችን ስፔስፊኬሽን ያዘጋጃል።
13. የተቋማትን አቅም ለመገንባት የIDP (Institutional Development Plan) አዘገጃጀት ሥልጠና ይሰጣል።
በሰልጣኝ፣ አሰልጣኝ፣ አመራር ልማት እና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት የሚሰጡ ዋና ዋና አገልግሎቶች
የዕቅድ ዝግጅት እና የሥልጠና ሥርዓት ተግባራት
1. ዳይሬክቶሬቱ የረጅም እና የአጭር ጊዜ የሥራ ዕቅዶችን ያዘጋጃል፤ አፈጻጸማቸውንም በቅርበት ይከታተላል።
2. ወቅታዊ የሥራ ገበያ ፍላጎት ጥናት በማካሄድ፣ በሁሉም የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሚሰጠው ሥልጠና በገበያ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያረጋግጣል።
3. ደረጃውን የጠበቀ የመሠረታዊ፣ የመለስተኛና የመካከለኛ የቴክኒክና ሙያ ሥርዓተ-ትምህርት በማዘጋጀት ለሚመለከታቸው አካላት ያስተላልፋል፤ አተገባበሩንም ይከታተላል።
4. የማስተማሪያና ማሰልጠኛ መሣሪያዎችን (TTLM) እና ክልላዊ የአጫጭር ሥልጠና መስጫ ሞጁሎችን በማዘጋጀት ለተግባሪ አካላት ያሰራጫል።
5. የፖሊሲ እና የሕግ ማዕቀፎችን መሠረት በማድረግ ክልላዊ የሰልጣኞች ቅበላ መስፈርትን ያዘጋጃል፤ አፈጻጸሙንም ይከታተላል።
የሰልጣኞች ድጋፍ እና የትብብር ሥልጠና
1. ሰልጣኞች በቂ መረጃ ኖሯቸው የሙያ ምርጫ እንዲያደርጉና የተመቻቸ ሽግግር እንዲኖራቸው የሙያ ምክር (Career Guidance) አገልግሎት ይሰጣል።
2. የትብብር ሥልጠና መስጠት የሚችሉ ኢንዱስትሪዎችን በመለየትና አቅማቸውን በመገንባት ለሥልጠናው እንዲውሉ ያደርጋል።
3. በኢንዱስትሪዎች ውስጥ የሚገኙ አሰልጣኞችን በመለየትና የክህሎት ማሻሻያ ሥልጠና በመስጠት አቅማቸውን ያሳድጋል።
4. ሰልጣኞች በመደበኛና በአጫጭር ፕሮግራሞች ተግባር ተኮር ሥልጠና እንዲወስዱ በማድረግ የክህሎት ክፍተት ችግርን ይቀርፋል።
5. መደበኛ ባልሆኑ ዘርፎች ለተሰማሩ ሠራተኞች የክህሎት ማሻሻያ ሥርዓት ተደራሽ በማድረግ የሙያ ብቃታቸውን ያሳድጋል።
6.ሰልጣኞች በተቀመጠው የሰዓት ገደብ (Nominal Hour) መሠረት ተቋማዊ እና የመውጫ ምዘናዎችን መውሰዳቸውን ይከታተላል።
የአሰልጣኞችና የአመራር አቅም ግንባታ
1. የአሰልጣኞችና የአመራሮችን የክህሎት ክፍተት በመለየት በአጫጭር ሥልጠናዎች አቅማቸውን ይገነባል።
2. በክረምትና በበጋ ፕሮግራሞች አሰልጣኞችና አመራሮች በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ የሙያ ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ ምልመላ ያካሂዳል።
3. በብቃት ማረጋገጫ ምዘና ለበቁ አሰልጣኞች የማሰልጠን ሥነ-ዘዴ (Pedagogy) ሥልጠና በመስጠት ሥራ ላይ መዋሉን ይከታተላል።
በቴክኖሎጂ ምርምር ሽግግር እና የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ዳይሬክቶሬት የሚሰጡ ዋና ዋና አገልግሎቶች
የቴክኖሎጂ ሽግግርና የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ተግባራት
1. ዳይሬክቶሬቱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የረጅምና የአጭር ጊዜ የሥራ ዕቅዶችን ያቅዳል።
2. በተመረጡ የትኩረት ዘርፎች ላይ ተግባራዊ ጥናትና ምርምር እንዲሁም የእሴት ሰንሰለት ትንተና ጥናቶችን ያካሂዳል።
3. ቴክኖሎጂዎችን በስፋት የሚያባዙ ኢንተርፕራይዞችን በመለየት በሥልጠና የማብቃት ሥራ ይሠራል፤ ለዚህም የሚያገለግሉ ሥርዓተ-ሰነዶችን በማዘጋጀት ሥልጠና ይሰጣል።
4. የቴክኖሎጂና የፈጠራ ባለቤቶች እንዲበረታቱ ለማድረግ የአዕምሯዊ ንብረት ባለቤትነት ጥበቃ መብት (Intellectual Property Rights) እንዲያገኙ ያመቻቻል።
5. የተሠሩ ቴክኖሎጂዎችን የጥራት ኦዲት በማድረግ የፈጠራና የማምረቻ ማዕከላትን እንዲሁም የዕውቀትና ክህሎት ሽግግር ማበልጸጊያ ማዕከላትን ያደራጃል።
የኢንተርፕራይዞች ድጋፍና የክህሎት ግንባታ
1. ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ውጤታማ ድጋፍ ለመስጠት እንዲቻል፣ በሥራ ላይ ያሉና ድጋፍ የሚደረግላቸውን ኢንተርፕራይዞች ኦዲት ያደርጋል።
2. በድጋፍ ማዕቀፎች አማካኝነት የክህሎት ክፍተቶችን በመለየት የአቅም ግንባታ ድጋፍ ይሰጣል።
3. በኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ አማካኝነት በመጡ ለውጦችና ውጤቶች ላይ የፋይዳ ዳሰሳ ጥናት ያካሂዳል።
4. የቴክኖሎጂ ሲምፖዝየም፣ ኢግዚቢሽን፣ ባዛር እንዲሁም የሐሳብና የክህሎት ውድድሮችን በማዘጋጀት የፈጠራ ሥራዎችን ያስተዋውቃል።
የመረጃ አያያዝ እና ክትትል
1. የተፈላጊ ቴክኖሎጂዎችን የመረጃ ምንጭ በማፈላለግ የቴክኖሎጂ ሰነዶችን ያደራጃል፤ እንዲሁም መረጃዎቹን በመረጃ ቋት (Database) ውስጥ ያከማቻል።
2. በዘርፉ ያሉ አንቀሳቃሾችን በደረጃ 4 ወይም በደረጃ 5 (Master Craftsman) በማብቃት የሥራ ሂደቱን በባለቤትነት እንዲመሩ ያደርጋል።
3. በሁሉም የሥራ እንቅስቃሴዎች ላይ ተከታታይነት ያለው ድጋፍና ክትትል በማድረግ አስፈላጊውን ግብረ-መልስ ይሰጣል።