መጋቢት 10/2018 ዓ.ም
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ ባለፉት 100 ቀናት ያከናወናቸውን ተግባራት አፈጻጸምና በቀጣይ 120 ቀናት ዕቅድ ላይ ያተኮረ ውይይትም አካሂዷል
ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አበባየሁ ታደሰ በዘርፎች በቀረበው ሪፖርትና በቅርቡ ባከናወኑት የመስክ ምልከታ መነሻ ባለፉት 100 ቀናት እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ በተደረገ የተቀናጀ ርብርብ አበረታች ውጤቶች መመዝገቡንም ገልጸዋል።
በተለይ በባዮሜትሪክስ የዜጎች ምዝገባ ረገድ የታየው ፈጣን ለውጥ የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመው ቀደም ሲል በመመዝገቢያ ኪት እጥረትና በተለያዩ ምክንያቶች ዘግይቶ የነበረው አፈጻጸም በቀጣዮቹ 120 ቀናት ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት ሊከናወን እንደሚገባ አሳስበዋል።
የግብርናው ሥራ እሴት የሚጨመርበት (Value addition) እና ከአካባቢ አልፎ ለዓለም አቀፍ ገበያ የሚቀርብ እንዲሆን በማድረግ ለወጣቶች የሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎች ዘላቂና ውጤታማ እንዲሆኑ በትኩረት መሰራት እንደለበት ተመልክቷል።
በተጨማሪም በህገወጥ የንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ (ኢ-መደበኛ የመንገድ ዳር ነጋዴዎች) የመሥሪያ ቦታና የብድር አቅርቦት በማመቻቸት ወደ መደበኛ የንግድ ሥርዓት እንዲገቡ የማድረግ ሥራ በስፋት መከናወን እንዳለበትም ተገልጿል።
የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችን የውስጥ አቅም ማጠናከር ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር አበባየሁ ኮሌጆች በግቢያቸው ውስጥ የሚገኙ ማሳዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ እንዲያውሉና የተለያዩ የቴክኖሎጂ ስራ ውጤቶችን ወደ ገቢ ምንጭ በመቀየር ራሳቸውን በኢኮኖሚ ማጠናከር እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የውጪ ሀገር የሥራ ስምሪት አፈጻጸምን በማጠናከር የዜጎችን ደህንነት ማረጋገጥና በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የተጠናከረ ቁጥጥር ማድረግ የቢሮው ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑም አጽንኦት ተሰጥቶበታል።
በመጨረሻም በቀጣይ 120 ቀናት ለወጣቱ የስራ ዕድል መፍጠር፣የብድር አመላለስና ስርጭት እንድሁም ቁጠባ ሥርዓትን ማሳለጥ፣ አጫጭር ሥልጠናዎችንና የምዘና ሥራዎችን በጥራት ማከናወን፣የቴክኖሎጂ ውጤቶችን (ማሽነሪዎችን) አምርቶ ለገበያ ማቅረብ እንዲሁም የዜጎችን የስራ ደህንነት ማስጠበቅ እንደሚገባ ተገልጿል።



