“ፈጠራና ቴክኖሎጂ ለሀገር ልማትና ብልጽግና በሚል መሪ ቃል በወላይታ ሶዶ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በፈጠራ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ልማትን በማፋጠን ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶችን ለማጠናከር ያለመ የቴክኖሎጂ ኤግዝቢሽን በይፋ ተከፍቷል።
በኤግዝቢሽኑ፣ በክላስተሩ ስር የሚገኙ አረካ፣ ገሱባ፣ በሌ፣ ጠበላ እና ሶዶ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች ያበለጸጓቸውን የፈጠራ ሥራዎችና የምርምር ውጤቶች ለሕዝብ እይታ እንደሚያቀርቡም ተመላክቷል።
በመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ኃላፊ አቶ በዛብህ ገበየሁ የሀገራት ውድድር እና እድገት በፈጠራና በቴክኖሎጂ አቅም እንደሚለካ ገልጸው፣ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ችግር ፈቺ ዜጎችን በማፍራት ረገድ የጎላ ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የኤግዝቢሽኑ ዋና ዓላማ የፈጠራ ባለቤቶችን ለማበረታታት፣ የተፈጠሩ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሀብት ለመቀየር እና ለማህበረሰቡ የሚጠቅሙ ውጤቶችን ለማስፋፋት እንደሆነም ኃላፊው ተናግረዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ልዩ ትኩረት እየተሰጠ መሆኑን ያስታወሱት ኃላፊው፣ በተለይም በኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በጋርመንትና ሌዘር ዘርፎች ላይ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን የማፍለቅና የማስፋፋት ሥራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ለማህበረሰቡ ጥቅም የሚውሉ ፈጠራዎችን ማበረታታትና ማስፋት የሀገርን ኢኮኖሚያዊ እድገት ከማፋጠን ባለፈ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ በቀጥታ ለማሻሻል የሚያስችል ቁልፍ መንገድ መሆኑንም አቶ በዛብህ ጠቅሰዋል።
የሶዶ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዋና ዲን ኢንጅነር ያዕቆብ ያሲን በበኩላቸው፣ በከተማዋና በአካባቢው የሚስተዋሉ የማህበረሰቡን ችግር የሚቀርፉ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸው፣ የተማሪዎችና የመምህራን ፈጠራዎች ከመማሪያ ክፍል ባሻገር ወደ ምርትና ገበያ እንዲገቡ ተቋሙ በትኩረት እየሠራ መሆኑንም አብራርተዋል።
በዚህም የኮሌጁ የመኪና ማሰልጠኛ ማዕከል እና የዳቦ ማምረቻ በይፋ ሥራ መጀመራቸውን ጠቁመው፣ ምርቶቹ ለማህበረሰቡ ሽያጭ መቅረብ መጀመራቸውን አስታውቀዋል።
ተቋሙ የሚሰጠው ስልጠና በክህሎት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን በማድረግ፣ ሰልጣኞች በተግባር አምርተው በመሸጥ ገቢ እንዲያገኙ እና ከስልጠና በኋላ ራሳቸውን ችለው ወደ ሥራ ዓለም እንዲገቡ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ገልጸዋል።
በኤግዝቢሽኑ ውስጥ ለኢንዱስትሪ ድጋፍ የሚያደርጉ ማሽኖች፣ ለእርሻ ሥራ የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎች፣ ለአካባቢ ጥበቃ እና ለኃይል አጠቃቀም የተቀየሱ ፈጠራዎች እንዲሁም ለማህበረሰቡ ችግሮች ተግባራዊ መፍትሄ የሚሰጡ ውጤቶች የቀረቡ ሲሆን ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ መሆኑም ታውቋል።


