በክልሉ ሁለተኛ የሆነው የአርባምንጭ መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ተቋም ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በአርባ ምንጭ ከተማ በተካሄደው የ«መሶብ» የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከል ምረቃ እና ይፋዊ ስራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ይህ ስራ መጀመሩ በክልሉ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን ገልፀዋል። «መሶብ» የአንድ ማዕከል አገልግሎት በተበታተነ መልኩና በባህላዊ አሰራር ሲሰጡ የነበሩ በርካታ የመንግስት አገልግሎቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በማስደገፍ በአንድ ጣሪያ ስር የሚያስተሳስር በመሆኑ፣ ለዘመናት ህብረተሰቡን ሲያማርሩ የነበሩ የቢሮክራሲ ማነቆዎችን ሙሉ በሙሉ እንደሚፈታ ገልጸዋል። ይህ ማዕከል ዜጎች ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና አላስፈላጊ ወጪያቸውን እንዲቆጥቡ ያደርጋል ብለዋል። ኢንሼቲቩ የመንግስትን አገልግሎት ተደራሽነትና ቀልጣፋነት ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር የህዝብን እርካታ እንደሚያረጋግጥ ያብራሩት ሲሆን ማዕከሉ የብልሹ አሰራርና የሙስና ስጋቶችን በመቅረፍ ረገድ ያለውን ሚና ከፍተኛ መሆኑንም አብራርተዋል። የ«መሶብ» ሥርዓት ሙሉ በሙሉ በዲጂታል መሠረተ ልማትና በቴክኖሎጂ የተደገፈ በመሆኑ፣ የአገልግሎት ሰጪና የነዋሪዎችን ቀጥተኛ ንክኪ በመቀነስ የአገልግሎት አሰጣጡን ግልጽ፣ ተጠያቂነት የሰፈነበትና ከሙስና የጸዳ እንደሚያደርገውም ርዕሰ መስተዳድሩ አመላክተዋል። እንደ ብሔራዊ መታወቂያ፣ የኢሚግሬሽን፣ የንግድ ፈቃድና ኢንቨስትመንት ያሉ ወሳኝ አገልግሎቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ በጥራት ማቅረብ መቻሉ በክልሉ ምቹ የቢዝነስና የኢንቨስትመንት ከባቢ ለመፍጠር ትልቅ አቅም እንደሚሆንም ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ጠቅሰዋል። ዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት መዘርጋቱ ብቻውን በቂ እንዳልሆነ በመግለጽ፣ በማዕከሉ የሚመደቡ አመራሮችና ባለሙያዎች የህዝብ አገልጋይነት ስሜትን በተግባር ሊያሳዩ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበው ይህንን የተቀናጀ አሰራር በላቀ የኃላፊነት ስሜትና በታማኝነት በመምራት የክልሉን ነዋሪዎች የዘመናት የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በዘላቂነት መመለስ እንደሚገባ አሳስበዋል። መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከል በቀጣይም ከሁለት ቀናት በኋላ በዲላ ከተማ የሚመረቀውን ጨምሮ ወደ ሌሎች የክልሉ ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች በማስፋፋት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሠራም ተናግረዋል።የኢፌዴሪ ሲቭል ሰርቪስ ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር ወ/ሮ አልማዝ መሰለ በበኩላቸው የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ራዕይ ከማሳካት አንጻር እስካሁን 51 የመሶብ አንድ ማዕከላት በ11 ክልሎችና በ2ቱ ከተማ መስተዳድሮች ተመርቀው ወደ ስራ የገቡ ሲሆን ዛሬ የሚመረቀው የአርባምንጭ ማዕከል ሲጨመር ቁጥሩን 52 እንደሚደርስ ገልፀዋል። በክልሉ ከወላይታ ሶዶ ማዕከል ቀጥሎ የአርባምንጭ መሶብ 2ኛው ወደ አገልግሎት የገባ ማዕከል መሆኑን አመላክተው ይህም ሃገራችን አገልግሎቶችን ተደራሽ እና ግልጽ ከማድረግ አንጻር ከፍ ያደርጋል ብለዋል።የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኢኒሼቲቭ የሆነው የመሶብ ፕሮጀክት በህንፃዎች ወይም በቴክኖሎጂ ብቻ የታጠረ ሳይሆን የብልጽግና ፓርቲ እና የመንግስታችን መርሆዎች መሠረት ያደረገ ሰው ተኮር የአገልግሎት ልህቀትን ማረጋገጥና ዜጎችን ማክበር ነው ሲሉም ወይዘሮ አልማዝ አብራርተዋል። የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዜጎች ከመንግስት የሚፈልጓቸውን አገልግሎቶች በአንድ ቦታ ላይ በክብር እና በቅልጥፍና የሚያገኙበት ሥርዓት ነው ብለዋል።መሶብ የአንድ ማዕከል ዜጋ የሚፈልጋቸውን አገልግሎቶች እንደ ዜግነት መብቱ ለማግኘት በፍትሃዊነት እና በውጤታማነት እንዲስተናገድ የሚደረግበት ሥርዓት መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ኮሚሽነሯ በቀጣይነት ወደ ሌሎች መዋቅሮች የሚሰፋ መሆኑን ገልፀዋል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ሙልቀን ቃሬ በበኩላቸው ይህ ማዕከል የዲጂታል ሕልም ፍቺ ነው ያሉ ሲሆን መንግስት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የገባውን ቃል መተግበሩን የሚያሳይ ምስክር መሆኑን አስገንዝበዋል። የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) በአርባ ምንጭ መሶብ የአንድ ማዕከል አራት የፌደራል እና አምስት የክልሉ ቢሮዎች 32 አገልግሎቶች እንደሚሰጡ ገልፀው ከዚህ በፊት ዜጎች የሚገጥማቸውን እንግልት በጥራትና ፍጥነት የሚሰጥ መሆኑንም ጠቅሰዋል።በሩፋኤል ግርማይ

