በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሳይበር ደህንነት ላይ ትኩረት ያደረገ ስልጠና በአርባምንጭ ከተማ እየተሰጠ ይገኛል ።
ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደገለፁት ፣ኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት የተለያዩ ተግባራት እያከናወነች ስለመሆኗ ጠቁመዋል ።
ዲጂታል ኢኮኖሚ ወጣቱን ትውልድ ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው ፣የኢትዮጵያ ወጣቶችም በዘርፉ በቂ እውቀት እንዲኖራቸው መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የወጣቶችን ልዩ ተሰጥኦ በማዳበር በዲጂታሉ ዓለም ሀገራቸውን ማሳደግ እንደሚገባቸውም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል ።
ጠንካራ የደህንነት ስርዓት በመገንባት ብሔራዊ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ እንደሚገባ የገለፁት ዶክተር አበባየሁ የኢትዮጵያ የመረጃ ደህንነት አስተዳደር የሀገሪቱን ከፍታ እያረጋገጠ ያለ ተቋም ነው ብለዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ጀነራል ትዕግሥት አሚም በበኩላቸው፤ በሀገሪቱ የሳይበር ደህንነት ምህዳርን በማስፋፋት ብሔራዊ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ከተለያዩ አካባቢዎች የሚሰነዘሩ የሳይበር ጥቃቶችን ለመከላከል አስተዳደሩ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየሰራ መሆኑን ገልፀው ፣ስልጠናው ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመደገፍ እንደሚያግዝ አስረድተዋል ።
የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ ቦጋለ ቦሼ (ዶ/ር)፤ በክልሉ ዲጂታል ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
አገልግሎቱ በፋይናንስ ስርዓት ውስጥ ደህንነቱ የተጠበቀ ግብይት እንዲኖር ከማስቻሉ ባለፈ ዜጎች ዲጂታል አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን ዶክተር ቦጋለ አስገንዝበዋል ።
በቀጣይም በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን ከዲጂታል ኢኮኖሚ ጋር በማስተሳሰር የህዝቡን ተጠቃሚነትን ይበል ለማረጋገጥ ይሰራል ብለዋል።
የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ከመረጃ ደህንነት አስተዳዳሪ ጋር በጋራ በመሆን እየተሰጠው ባለው ስልጠና፣ የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ ።


