የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) በወላይታ ዞን በተለያዩ አካባቢዎች የስራ ዕድል ፈጠራን ጨምሮ ሌሎች እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች ምልከታ አድርገዋል
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) የክልሉ መንግስት ከአምስቱ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ምሦሦዎች የኢንዱስትሪ ዘርፍ አንዱ ነው ብለዋል።
ክልሉ ለዚህም ፀጋ ትልቅ አቅም ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ክህሎት መሪ የስራ ዕድል የመፍጠር ተግባራት ማከናወን እንደሚገባ ጠቁመዋል ።
ወጣቶችን በኢንተርፕራይዝ በማደራጀት ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ ዶክተር አበባየሁ ገልጸዋል ። የክልሉ መንግስት በተለይ በኢንተርፕራይዝ ለተደራጁት ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ማሰራጨቱንም አስረድተዋል ።
በሌላ በኩል የቴክኒክ ፖሊ ኮሌጆች የኢንተርፕሪነር መፈልፈያ ማዕከል መሆን እንዳለባቸው ጠቁመው በኮሌጁ ባገኙት ስልጠና ብቁና ተወዳዳሪ እየሆኑ ነው ብለዋል።
በክልሉ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት እንዲያገኙ በተከናወነው ተግባራት ውጤት መመዝገቡንም ዶክተር አበባየሁ ጠቁመዋል ። በሀገሪቷ ያለውን የስራ አጥ መጠን ለማወቅና የገበያ አማራጮችን ማቀፍ የሚችል ስራዎች ታሳቢ ያደረጉ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመው፣ባለፉት ስድስት ወራት ከ7 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት መፈጠሩንም አስታውቋል ።



